• የቤተክርስቲያኑ መንፈሣዊ አገልግሎት
  • የቤተክርስቲያኑ መደበኛ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚካሔደው እሑድ እሑድ ከ14፡00 -18፡00 ባለው ጊዜ መካከል ነው፡፡ ሐሙስ ዕለት ከ11፡00-13፡30 ለቤተክርስቲያኑ ጠቅላላ አገልግሎት የሚፀለይበት ጊዜ አለው፡፡ ከዚህ ውጭ ወደ 12 የሚደርሱ ያገልግሎት ዘርፎች ሲኖሩት፣ እነዚህም መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የዕለት ተዕለት ኘሮግራሞቻቸውን ተከትለው በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ይካሄዳሉ፡፡ እነዚህም፡- የመንፈሣዊ አገልግሎት፣ የፀሎት፣ የፋይናንስ፣ የእህቶች፣ የወንድሞች፣ የወጣቶች፣ የሰንበት ት/ቤት፣ የመዘመራንና የአምልኮ አገልግሎት፣ የወንጌል ማዳረስ አገልግሎት፣ የዲቁና፣ የሥነጽሑፍና የሚዲያ፣ የጽዳትና የምግብ ዝግጅት አገልግሎት፣ ዘርፎችና ንዑሳን ዘርፎች ናቸው፡፡
  • ቅዱሣት አገልግሎቶች
    • የጥምቀት ሥርዓት
  • ቤተክርስቲያኗ በሕፃናትና በአዋቂዎች ጥምቀት ስለምታምን በቅዱስ ጥምቀት አማካይነት፣ በአባላት ጥያቄና በደንቡ መሠረት በአንዲት ጥምቀት በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስቅዱስ አንድ አምላክ ስም መጠመቃቸውን አምና ሥርዓቱን ትፈጽማለች፡፡ ሕፃናትንም በፀሎት ለጌታ አሳልፋ ትሰጣለች፡፡
    • የጌታ እራት/ቅዱስ ቁርባን

መሠረታዊ የጥምቀትና የክርስቲና ትምህርት ተከታትለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መዳናቸውን ያረጋገጡ አባላት የጌታ እራት እንዲካፈሉ ይደረጋል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱም ሥርዓቱን ትፈጽማለች፡፡

    • ቅዱስ ጋብቻ

ክርስቲያናዊ ጋብቻ በአንድ ወንድና ሴት መካከል የሚፈጸም ቅዱስ ሥርዓት መሆኑን ቤተክርስቲያናችን ስለምታምን የቤተክርስቲያኑ አባል ተጋቢዎች በሚያቀርቡት የጋብቻ ጥያቄ መሠረት ሥርዓቱን ትፈጽማለች፡፡

    • የሰንበት /ቤት

በየእሑድ ለሕፃናት የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ሕፃናት በእግዚአብሔር ቃል ዕውነት ተኮትኩተው ማደግ እንዲችሉ ቤተክርስቲያን ለሕፃናት ልዩ ትኩረት ትሰጣለች፡፡

    • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

የቤተክርስቲያኑ አባላት ሕያው ቃሉን በግልና በኀብረት እንዲያጠኑ ታበረታታለች፡፡ ይኸም ለመንፈሣዊ ሕይወት ኑሮ መሪና ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ፡- በእምነት ለማደግም ጭምር መሠረት መሆኑን በማመን፣ አባላቶችዋ ተቀራርበው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የጥናት ቡድኖችን በማደራጀት አገልግሎቱ እንዲካሄድ ታደርጋለች፡፡

  • የቤተክርስቲያኑ በጀት/ስለመስጠት

ቤተክርስቲያኗ በየዓመቱ ለሥራዋ አገልግሎት የሥራ ማስኬጃ በጀት ትመድባለች፡፡ ዋና ገቢዋ ከአባሎችዋ በሥጦታ የሚሰበሰብ ገንዘብ ሲሆን፣ ከሌሎች ከውጭ አካላትም ከሚገኙ ገቢዎችም ጭምር ነው፡፡ ማንኛውም ገቢና ወጪ በበጀትዋ መሠረት እየተዳደረ በሥራ ላይ ይውላል፡፡ ከውስጥም ይሁን ከውጭ የሚሰበሰቡ የቤተክርስቲያኒቱ በጀት በባንክ ሂሣብዋ ይንቀሳቀሳል፡፡ መዋጮ ወይም ዕርዳታ ማድረግ የሚፈልጉ ማናቸውም አካላት የቤተክርስቲያኒቱን የባንክ ሂሣብ መጠቀም ይችላሉ፡፡ የሂሣብ ቁጥሯ በቤተክርስቲያኑ የመረጃ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል፡፡

  • የቤተክርስቲያኒቱ የወደፊት ራዕይ፣ ተልዕኮዋና ኃላፊነት

የሻሎም ቃል ኪዳን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ራዕይዋ፣ ተልዕኮና ኃላፊነትዋ ባጭር የሚከተለው ነው፡፡

  • ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኝ አድርገው የወሰኑ ደቀመዛሙርትን ማሠልጠን ለአገልግሎት ማዘጋጀት፣ አገልጋዮችን ማፍራት
  • ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር የጀመረውን የታላቁን ተልዕኮ አገልግሎት ለመፈጸም መትጋት፡-
  • ከእግዚአብሔር አብ፣ ከእግዚአብሔር ወልድ፣ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የፍቅር ሥራ ጋር ኀብረት ማድረግ፣ ይህንንም ለሌሎች ማሣየት፣ ፍቅርና አንድነትን በመሪዎችና በምዕመናን መካከል እያደገ እንዲሄድ መጣር፡-
  • የታላቁ ተልዕኮ አገልግሎት በከተማዋና በአካባቢው ለመፈጸም መትጋት፣ (ማቴ 28 19-20) ሰዎች ወንጌልን እንድሰሙና እንድዲኑ የምሥራቹን ቃል ማሰማትና የዳኑትም ክርስቶስን ወደመምሰል እንድያድጉ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንድችሉ ማስተማር
  • ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር የፈጸማቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተልዕኮ በመከተል ሰዎችን በሥጋም በነፍስም ማገልገል፡- (Wholisticc Services)
  • እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያናችን የሰጠውን ተስፋና ኪዳን ከግብ ለማድረስ፣ ለመፈጸም መሥራት፡-
  • ምሥጋናና አምልኮን ለእግዚአብሔር መስጠት፣ የመንፈስቅዱስ ሥጦታዎችን እንደ እግዚአብሔር ቃል በጥንቃቄ ተግባራዊ ማድረግ
  • ዶክትሪናል የሆኑ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎችን፣ ቅዱሳት አገልግሎቶችን በቤተክርስቲያኑ መተግበር፡- ለምሣሌ ሥልጣን ያለው የቃሉ አገልግሎት፣ የጌታ እራት (ቅዱስ ቁርባን)፣ ቅዱስ ጥምቀት፣ ቅዱስ ጋብቻ፣  የመሣሠሉት ናቸው፡፡
  • የእግዚአብሔር መንግስት ለማስፋት፣ ለወንጌል ሥራ እገዛ የሚያደርጉ ሥጦታዎችን በገንዘብ መልክ ማሰባሰብ ለምሣሌ መባ፣ የፍቅር ሥጦታ፣ አሥራት የመሣሠሉት ናቸው፡፡
  • ለቤተክርስቲያኑ አገልግሎት መታነጽና ዕድገት የሚረዱ ልዮ ልዮ የአገልግሎት ቡድኖችን ማቋቋምና ማጠናከር፡- እነዚህም የወጣቶች፣ የእህቶች፣ የሰንበት ት/ቤት፣ የመዘመራን ቡድን፣ የፀሎት ፣ የአምልኮ ፣ የቤት ለቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ሌሎችንም ያካትታል፡፡
  • በበርገን ከተማና በአካባቢው ካሉት ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ጋር ኀብረት መፍጠር፡-
  • ከሰንትራል ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር የጋራ የክርስቲያን ኃላፊነት መወጣት፣ በአገልግሎቶች በመሣተፍ፣ ሙሉውን ሰው በማገልገል ተግባር በጋራ መሥራት ለወንጌል ሥርጭት አስፈላጊ ዜዴዎችን ማስፋፋት፡- ለፍሬአማ አገልግሎት ስለሚረዳ ነው፡፡